ክርስትና እና እንስታዊነት ሆድና ጀርባ በሲራክ ተመስገን

የእንስታዊነት (Feminism) እንቅስቃሴ በመሰረታዊነት ሴቷን ከወንዱ እኩል በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካው መስክ ተሳታፊ እንድትሆን ማስቻል ነው። ሴቷ በፆታዋ ብቻ የሚደርስባትን መገፋት ለማስቀረት መንቀሳቀስ ነው። የእዚህ መገፋት እና አባታዊ ስርዓት በአለም ላይ መዘርጋት ክርስትና ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብዬ አምናለሁ። ለእዚህም ነው ብዕሬን ያነሳሁት። እንግሊዛዊው የባይዎሎጅ ሊቅ ሪቻርድ ዳውኪንስ ብዙ በተነገረለት ‘The God Delusion’ በተባለው ድንቅ መጽሀፉ ላይ የብሉይ ኪዳኑን አምላክ እንዲህ ሲል በምሬት ይገልፀዋል፡

“The God of the Old Testament is arguably the most unpleasant character in all fiction: jealous and proud of it; a petty, unjust, unforgiving control-freak; a vindictive, bloodthirsty ethnic cleanser; a misogynistic, homophobic, racist, infanticidal, genocidal, filicidal, pestilential, megalomaniacal, sadomasochistic, capriciously malevolent bully”

ፕሮፌሰር ዳውኪንስ ይሄን ሲል ግን እንዲሁ በባዶው አይደለም፤ ለእያንዳንዱ ስያሜው ከብሉይ ኪዳን መጻህፍት ጥቅስ እያጣቀሰ እንጅ፡፡ እኔም ‹‹ይሄንን ኢ–ሰብዓዊ የሆነን አካል በአምላክነት የተቀበለ ሰው ስለ መብት ሊያወራ አይገባም ›› የምለውም በመጽሃፉ የተጠቀሰው ባህርይ እጅግ ከሰብዓዊነት የራቀ በመሆኑ ነው፡፡። በዚህ ርዕስ የማነሳው የሴቶች መብት እና የእንስታዊነት (Feminism) ጉዳይም የመጽሐፉ ዋነኛ ተጠቂ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች ከብሉይ ኪዳን እስከ አዲስ ኪዳን ድረስ ሴቶች ተጨቋኝ ሆነው የቀረቡበት ጥራዝ ነው። አብነት እየጠቃቀስኩ ላስረዳ፡፡

የብሉይ ሴቶች

በብሉይ በእግዚአብሔር ተወዳጅ ከሆኑ ነገስታት አንዱ ንጉስ ዳዊት ነው። ይህ ሰዉ ወሲብ በጣም ይወድ ነበረ። ብዙም ዕቁባቶች ነበሩት። ሴቶችንም እንደግል ንብረቱ ቆጥሮ በአንድ ቤት ዘግቶ፣ ከማንም ሳይገናኙ እንዲሞቱ የማድረግ ስልጣን ነበረው ዳዊት (2ኛ ሳሙኤል 20:3)፡፡ በአመት ሶስት ጊዜ በሚደረገው የቂጣ በዓል፣ የመኸር በዓል እና የመክተቻ በአል ወቅት በእግዝአብሔር ፊት ለዕይታ የሚቀርቡት ወንዶች ብቻም ነበሩ (ዘጸአት፣ 23:14–17)፡፡ በሙሴዎ ዓለም የተፈጥሮ ኡደቶች (ወሊድም ሆነ የወር አበባ) ለሴት ልጅ የመርከስ ምልክት ነው። እንደዚህም ሆኖ ወንድ ከወለደች 7 ቀን የረከሰች ነች። በአስገራሚ ሁኔታ ሴት ከወለደች ዕጥፍ ቀን የረከሰች ነች መባሏ ነው (ዘሌዋውያን 12: 1–5)፡፡እግዜሩ ለሰው ልጆች ዋጋ ማውጣቱ ሲገርም ሴቶች ከወንዶች ያነሰ ዋጋ ያለቸው መሆኑ ይበልጥ ያስቃል። በብሉዩ ዓለም ከአምስት አመት ሴት ልጅ ይልቅ የአንድ ወር ወንድ ህፃን በዋጋ ይበልጣል (ዘሌዋውያን 27: 1–7)፡፡ ይባስ ብሎም ሙሴ በአምላኩ ሕዝቡን እንዲቆጥር ሲታዘዝ ሴቶች እንደሰው አይቆጠሩም ነበረ (ዘኁልቆ 3:15)፡፡ በዚህ አያበቃም እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ህግ መሰረት አንድ ሰው ቢሞት ወንዶች ልጆቹ ብቻ የንብረት ወራሾች ይሆናሉ። ሴቶች ልጆች ወራሾች የሚሆኑት ሟች ወንድ ልጆች ከሌሉት ብቻ ነው (ዘኁልቆ 27:8–11)፡፡ ድንግልና ሳይኖራት ያገባች ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ‹የእግዚአብሔር ህግ› ያዛል (ዘዳግም22:13–21)። በተቃራኒው ወንድ ድንግልና ከሌለው ይቀጣ የሚል ህግ ግን የለም። በአጠቃላይ የብሉይ ኪዳን ዘመን ተብሎ በሚታወቀው ጊዜ ሴት እቃ ( ) ነች እንጅ ሰው አልነበረችም፡፡ አዲስ ኪዳኑስ ምን ይላል;

ሴቶች በአዲስ ኪዳን

ከብሉይ ኪዳኑ የጭካኔ ዘመን አንፃር እየሱስ ክርስቶስ አብዮተኛ ነበረ ማለት ይቻላል። በአይሁዳውያን ዘንድ ሴቶችን ዝቅዝቅ የማድረግ ባህልን ሲጠቀም አይታይም። ሴቶችንም ያስተምርም ነበረ። በተዘዋወረባቸው ቦታዎችም ሁሉ በቋሚነት አብረውት ይከተለት ነበረ። እንደ ወንዶቹ ይፈውሳቸውም ምሳሌ ያደርጋቸዋልም። ይልቁኑ የክርትና መሰረት ነው ተብሎ ከሚነገርለት ከቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ ነው አዲስ ኪዳኑ በሴቶች ላይ ሲጨክን የሚታየው፡፡ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 11:3 ላይ «ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ» ብሎ ሴትን በደረጃ ከወንዱ አውርዶ ያስቀምጣታል፡፡ አልፎም ለሴት ልጅ የፀጉር አቆራረጥ ህግ ያፀድቃል። ሴትም ለወንድ ሲባል የተፈጠረች እንደሆነ በግልፅ እና በጉልህ ይናገራል። ሚስቶች የባሎቻቸው ባሪያ እንደሆኑ እና ያለምንም ማመንታት ለባሎቻቸው እንዲገዙ ደንግጓል (ኤፌሶን 5:22–23)፡፡ ሴቶች ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ መናገር አይፈቀድላቸውም። ማወቅ የፈለጉት ነገር እንኳን ቢኖር በቤታቸው ባሎቻቸውን እንዲጠይቁ ነው እግዜሩ የሚያዘውይመክራል ጳውሎስ (1ኛ ቆሮንቶስ 14:34–36)፡፡ ሴቶች እንዲያስተምሩ አይፈቀድላቸውም። በወንድ ላይም መሰልጠን አይችሉም (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:11–15)፤ በማለትም ‹ወንድ ወደ ችሎት፤ ሴት ወደ ማጀትን›› ጳውሎስ ይሰብከናል፡፡ ሲያጠቃልልም ሴቶች ደካሞች መሆናቸው በ1ኛ ጴጥሮስ 3:7 ላይ ይነግረናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ እዚህ ላይ ነው ጥያቄው፡፡ ይሄን የመሰለ ሴቶችን እንደሰው እንኳን ለመቁጥር የሚግደረደር የጭቆና መሳሪያ ተይዞ ስለ ሴቶች መብት ማውራት እንዴት ይቻላል? መብትስ ምንድን ነው? ራስን መቃረን ደሞ በሽታ ነው። ይህን የሃይማኖት የጭቆና ህግጋት እና ትዕዛዝ አውልቀው ሳይጥሉ ‹እንስታዊት ነኝ› ማለት ለእኔ ለእንቅስቃሴው ስድብ ነው። እነደጳውሎስ ምክር ስጥ ብባልም እንደዚህ የመጽሃፉ አማኒያን ራሳቸው ‹የሴት መብት ተከራካሪ› ብለው የሚጠሩ ሰዎች ከእንስታዊነት እንቅስቃሴ ላይ እጃቸውን ቢያነሱ ሸጋ ነው ብይ ነኝ፡፡ “You can’t have your cake and eat it” እንዲሉ፤ ወይ ሽልጦውን ወይ ሆዳችንን ነው ጥያቄው፡፡ ለነገሩ እንደ ኤልዛቤት ስታንተን ያሉ ሴቶች ‘The Woman’s Bible’ ብለው ማሻሻያ ለማድረግ መነሳታቸው፤ የዚሁ የመጽሃፉ ጨቋኝነት ቢያማራቸው አይደለምን?

 

2 comments

 1. በመጀመሪያ የፀሐፊው አላማው ስለሴቶች እኩልነት ማቀነቀን ሳይሆን ፀሐፊው እንደኔ ግምት ኢአማኒ ስለሆነ ክርስትና ሴቶችን ይጨቁናል የሚለውን ነገር ለይቶ ማሳየት ይመስለኛል። ካልሆነ ግን ክርስቲያን የሆነ ሴት ስለ እኩልነት ማውራት አይገባትም (ብዬ አላምንም) የሚለው መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ሀርግ ፌሚንዝም ማለት ሴቶች በማህበራዊ ፣በፖለቲካ ፣በትምህርት፣ በሥራ እና በመሳሰሉት ከወንዶች እኩል ዕድል ይኑራቸው የሚለውን ሳይሆን ያንተን ኢአማኒያንነት አስርጎ የማስገባት አላማው ነው ሚታየኝ ። በመሰረቱ የሴቶችን እኩልነት እናራምዳለን የሚሉ አንዳንድ ሰዎችን (ምናልባትም ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ) የበታችነት ስሜት ማወራረጃ በደሉን ያሉትን ሰዎች መበቀል እንጂ በደሉን የማስቀረት አላማ የሌላቸው፣ ጉድለታቸው መደበቂያ ሲያደርጉት በተለያየ መልኩ አይቻለሁ ይሄ ነገር በየትኛውም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚታይ ነው በርግጥ።

  አሁን ግን ሃሳቤን ማስፈር የፈለኩት ክርስትናን ስለከሰስክባቸው ነገሮች ነው።

  1- “ንጉስ ዳዊት- ወሲብ በጣም ይወድ ነበረ ብዙም ዕቁባቶች ነበሩት። ሴቶችንም እንደግል ንብረቱ ቆጥሮ በአንድ ቤት ዘግቶ፣ ከማንም ሳይገናኙ እንዲሞቱ የማድረግ ስልጣን ነበረው”
  በመሰረቱ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈን ክፉም ደግም ታሪክ አለ የደጎችን ታሪክ ሰምተን አንብበን እንድንከተለው ከክፉ እና መጥፎ ታሪኮች ደሞ ተምረን ያን ከማድረግ እንድንታቀብ ምሳሌ እንዲሆንልን ነው የተጻፈልን። ቅዱስ ዳዊት ቅዱስ ያስባሉት ከጥፋቱ መፀፀቱ፣ ቀናኢ መሆኑ እና ሌሎች በጎ ምግባሮቹ እንጂ የእቁባቶቹ ብዛት ወይም የፈፀመው በደል አይደለም ስለዚህ ያነሳሃቸው ነገሮች የክርስትናን አስተምህሮ የሚያሳይ አይደለም። በመሰረቱ ትልቅ የመረዳት ክፍተት አያለሁ ምናልባትም ሀሳብህን የሚደግፍ መረጃ ፍላጋ እንጂ ሃሳቡ የመረዳት ፍላጎት ስለሌለህ ነው። እንደው የጠቀስቀው ምዕራፍና ቁጥር ላይ ያለውን ሃሳብ እንኩአን ብታየው አንተ ባቀረብቀው መልኩ ሚተረጎም አይደለም
  2ኛ ሳሙኤል 20:3”ዳዊትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤቱ መጣ፤ ንጉሡም ቤቱን ሊጠብቁ የተዋቸውን አሥሩን ቁባቶች ወስዶ ለጠባቂ ሰጣቸው፥ ቀለብም ሰጣቸው፥ ነገር ግን ወደ እነርሱ አልገባም፤ በቤት ተዘግተው እስኪሞቱም ድረስ ባልቴቶች ሆነው ተቀመጡ።” በቤት ተዘግተው ሚለውን እንዲመችህ አድርገህ ነው የተረጎምከው። እኔ እንደምረዳው ሌላ ሰው ሳያገቡ መኖራቸውን ነው እንጂ ከቤት እንዳይወጡ መዘጋታቸውን አይደለም።

  2- “በሙሴዎ ዓለም የተፈጥሮ ኡደቶች (ወሊድም ሆነ የወር አበባ) ለሴት ልጅ የመርከስ ምልክት ነው። እንደዚህም ሆኖ ወንድ ከወለደች 7 ቀን የረከሰች ነች። በአስገራሚ ሁኔታ ሴት ከወለደች ዕጥፍ ቀን የረከሰች ነች መባሏ ነው (ዘሌዋውያን 12: 1–5)፡፡”

  መርከስ የሚለው እዚህ ጋር ከደም መንፃት ጋር የተያያዘ ነው እንዲህ ነው የሚለው “ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ።ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ።” ከልጅ መውለድ ጋር ተያይዞ እናትየዋ ላይ የሚታየው የደም መፍሰስ እንደልጁ ፆታ ቆይታው ይለያያል (ሳይንስ ምን እንደሚል ማረጋገጥ አልቻልኩም ) ወንዶችና ሴቶች በተፈጥሮ ያለን ልዩነት ግልፅ ነው የሆርሞን መጠናችን የህዋሳችን አወቃቀር የሚፈጥረ ነገር ሊሆን ይችላል።

  3- “በብሉዩ ዓለም ከአምስት አመት ሴት ልጅ ይልቅ የአንድ ወር ወንድ ህፃን በዋጋ ይበልጣል (ዘሌዋውያን 27: 1–7)፡፡ ይባስ ብሎም ሙሴ በአምላኩ ሕዝቡን እንዲቆጥር ሲታዘዝ ሴቶች እንደሰው አይቆጠሩም ነበረ (ዘኁልቆ 3:15)፡፡”
  “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ። ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን። ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው።“ ሙሉ ቃሉ እንዲህ ይነበባል ሰው ለተሳለ ስለሰው ፈንታ የሚሰጠውን ዋጋ ነው ያስቀመጠው። በቤተመቅደሱ አገልግሎት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ጉልህ ድርሻ አላቸው ምናልባትም ከዛ የተነሳ ነው ወንድና ሴት የተሳለ የተለያየ እንዲከፍል የተደረገው። ሴት ለተሳለ ትንሽ እንዲከፍል መደረጉ ሴቶችን የበታች የሚያደርግበት መንገድ ግን ሊታየኝ አልቻለም።

  ሌላው ይሄን ነው ያነሳኸው “የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።” ይሄ ደሞ ሴቶች እንደሰው አለመቆጠራቸውን ሳይሆን የሌዊ ነገድ በወንድ በኩል እንደተቆጠረ ነው ሚያሳየው። ክህነትን ከቤተ ሌዊ ለሚወጡ የሚሰጥ ሰለነበረ ወንዶቹ መቆጠራቸው ከዛ አንፃር ይመስለኛል። የሰው ዘር ሲቆጠር ግን በወንድ በኩል መሄዱ ያለ ልማድ ነው ለመቁጠር አመቺ እንዲሆን ከወንድ ወይ ከሴት በአንዱ ብቻ መሆኑ ነበረበት በወንድ በኩል ተቆጠረ። በሁለቱም ቢቆጠር ምን እንደሚመስል ሃሳብ ያለው ሰው ቢያሳየኝ ደስ ይለኛል።

  3- በዚህ አያበቃም እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ህግ መሰረት አንድ ሰው ቢሞት ወንዶች ልጆቹ ብቻ የንብረት ወራሾች ይሆናሉ። ሴቶች ልጆች ወራሾች የሚሆኑት ሟች ወንድ ልጆች ከሌሉት ብቻ ነው (ዘኁልቆ 27:8–11)
  “የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤።።” እዚህ ጋር ርስት የሚለው እራሱ ንብረት ብለህ አንደተረጎምከው ብቻ የተወሰነ ትርጉም ያለው አይደለም። ለምን እንደዚህ አይነት ስርአት እንደነበረ በዛ ጊዜ የነበረውን የሰዎች የአኗኗር ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል።

  4- “ ድንግልና ሳይኖራት ያገባች ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ‹የእግዚአብሔር ህግ› ያዛል (ዘዳግም22:13–21)።”

  እንዲህ ነው ሚለው እንግዲህ “ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለታቸው ይሙቱ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ።” አመንዝራን ሁለቱንም ይቀጡ ነበር። የአንተን ሃሳብ ሚደግፍ አይመስለኝም ምን አልባትም የወንድ ልጅ ድንግልና የሚያሳይ ተፈጥሮአዊ ምልክት ሥለሌለው ድንግልናውን ያጣ ይቀጣ የሚለውን አንተ እየፈለክ ያለው አይነት ማግኘት አልቻልክም።

  5- “ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 11:3 ላይ «ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ» ብሎ ሴትን በደረጃ ከወንዱ አውርዶ ያስቀምጣታል፡፡”
  “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” የመጨረሻው አባባል ላይ አተኩሬ ልመልስልህ “የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ” ይላል እንግዲህ አኛ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው ብለን ለምናምን ሰዎች የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር የሚለው ራስ ማለት የደረጃን ና የመበላለጥን ሁኔታ ነው የሚያሳየው ብለን አንቀበልም። ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ እንዲል ሔዋን ከአዳም መገኘቷን የሚያሳይ ነው። እዛው ምዕራፍ ላይ ትንሽ ወረድ ብለህ ብታነብ ይህን ታገኛለህ “ ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና። ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና። ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል። ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው።”

  6- “አልፎም ለሴት ልጅ የፀጉር አቆራረጥ ህግ ያፀድቃል። ሴትም ለወንድ ሲባል የተፈጠረች እንደሆነ በግልፅ እና በጉልህ ይናገራል። ሚስቶች የባሎቻቸው ባሪያ እንደሆኑ እና ያለምንም ማመንታት ለባሎቻቸው እንዲገዙ ደንግጓል (ኤፌሶን 5:22–23)፡፡ ሴቶች ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ መናገር አይፈቀድላቸውም። ማወቅ የፈለጉት ነገር እንኳን ቢኖር በቤታቸው ባሎቻቸውን እንዲጠይቁ ነው እግዜሩ የሚያዘውይመክራል ጳውሎስ (1ኛ ቆሮንቶስ 14:34–36)፡፡ ሴቶች እንዲያስተምሩ አይፈቀድላቸውም። በወንድ ላይም መሰልጠን አይችሉም (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:11–15)፤ በማለትም ‹ወንድ ወደ ችሎት፤ ሴት ወደ ማጀትን›› ጳውሎስ ይሰብከናል፡፡ ሲያጠቃልልም ሴቶች ደካሞች መሆናቸው በ1ኛ ጴጥሮስ 3:7 ላይ ይነግረናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡”

  ስለፀጉር የተነገረው ለወንድም ለሴትም ነው አንተ የሴቱን ብቻ አንብበህ ሊሆን ይችላል “ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?”

  “ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤” ይሄንን እንደባርነት አርገህ መተርጎምህ የጋብቻን ትርጉም የተረዳህበት መንገድ ያሳሳተህ ይመስለኛል። በፍቅር ላይ የተመሰረት መገዛት ነው እንጂ አንተ እንደምታስበው የሎሌና የጌታ አይነት አይደለም ምክንያቱም እዛው ላይ ወረድ ብሎ ባል ሚስቱን እንደራሱ አርጎ እንዲወዳት እራሱን አሳልፎ እንዲሰጥላት ተፅፏል ። ይሄ በባልና ሚስት መካከል ያለን መተሳሰር ነው ሚያሳይ ነው እንጂ የመገዛዛትን ሂደት አይደለም።

  ሌሎቹ ደሞ ከቤተክርስትያ ሥርአት ጋር (በክህነት፣ በማስተማር) የተያያዘ እንጂ ህዝብ በተሰበሰበበት ፈፅሞ እንዳይናገሩ የሚል አይደለም። የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት የምትቀበለው የ ኢ/ኦ/ ቤተክርስቲያን ያላትን ሰርአት ማየት እንዴት ይሄ ቃል አንደሚተገበር ያሳየናል። በመድረክ ማስተማርና የክህነት አገልግሎት ለ ሴቶች አልተሰጠም ይሄም በምክንያት ነው የሆነው ለምን የሚለውን መልስ አብሮ ተቀምጧል። ሴቶች ግን ፈፅሞ ማስተማር እንዳልተከለከሉ ወንበር ዘርግተው ከሚያስተምሩት እንደነ እማሆይ ኅሪት ያሉትን እናቶች መጥቀስ ይቻላል።

  ባጠቃላይ ስለዚህ ፅሁፍ ልለው የምችለው መቼም የፃፍከው ሴቶችን እምነት ብለው የያዙት ክርስትና እንዴት እንደሚጨቁናቸው ለማሳየት ብታስብም ምክንያታውነት የሌለው ትርጉሙን ያልተረዳ መከራከሪያህ ይዘህ ነው የቀረብከው። ለእውቀት ሳይሆን ለመከራከር በጭፍን ጥላቻ የሚደረግ ንባብ ከዚህ የተሻለ መረዳት ላይሰጥህ እንደሚችል ግልፅ ነው።

  Liked by 1 person

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s